የእንቆቆዉ ቅማንት የስም አመጣጥና የዘመነ መሳፍንት ዉድቀት

የቅማንት ህዝብና የኢትዩጵያ አንድነት ታሪክ ከ1632-1868 ዓ.ም
የሃገራችን ጥንታዊ ኢትዩጵያ ማዕከላዊ መንግስት ዋና ከተማ ከዛጎየ ስርኦ መንግስት ዋና ከተማ ላሊበላ ከወደቀችበት ከ1270 ዓ.ም እስከ 1632 ዓ.ም ማዕከላዊ መንግስቱ ቋሚ ዋና ከተማ ሳይኖረዉ በተንቀሳቃሽ ቤተ-መንግስት ( Mobile court) ሃገሪቱን ሲያስተዳድር ከቆየ በኃላ በ16ኛዉ ክፍለ ዘመን በቅማንቶች ርስት ምድር ጓኣንደር ላይ ቋሚ የመንግስት መቀመጫ መሰረቱ፡፡ (በነገራችን ላይ ጓንግ(ኣ)ዳር ማለት በጥንታዊ አገዉኛና ቅማንትኛ ቋንቋ በሁለት ወንዞች መካከል ያለ ቦታ ማለት ሲሆን ይህዉም በአንገረብና ቀሃ ወንዝ መካከል ያለ ቦታ ማለት ነዉ፡፡                               ቀሀ ወንዝ” በመስኖ ተስቦ ለታሪካዊዉ ጥምቀተ መዋኛ ሲያገለግል    አንገረብ ወንዝ ግድብ                                                              ፕሮፊሰር ሰለሞን አዲስ የጎንደር ታሪክ ከጣሊያን ወረራ በኃላ አ.አ.ዩ (A.A.U) ይህ ጓኣንደር የሚለዉ ቃል በጊዜ ሂደት ጎንደር እየተባለ ተጠርቷል በሚል ጽፚል፡፡ በሌላ የቅማንት ህዝብ ባህላዊና ታሪካዊ ትዉፊቶች እንደሚስረዱት ከሆነ ደግሞ ጎንደር የሚለዉ መጠሪያ የተሰጠዉ ንጉስ ፋሲለደስ በአሁኑ ቦታ ቤተ-መንግስታቸዉን ከሰሩ በኃላ በግንባታዉ ሲሳተፉ የነበሩት ቅማንቶች ቦታዉ “ጎንደር” ብለዉ ጠሩት ይላል፤ ትርጉሙም “መናገሻ” ወይም “የጌታ መነሻ” ማለት ነዉ ፡፡ እንዲሚታወቀዉ የጎንደር ጥንታዊ ከተማ ሙሉ በሙሉ በቅማንት ህዝቦች የታጠረች እስትራቴጂክ ከተማ ነች፡፡ በሰሜን ወለቃና አንቾ ሚካኤል፤ በደቡብ ፀዳና አዘዞ፤ በምስራቅ ደፈጫ ኪዳነ ምህረትና ፈንጠር ፤ በምዕራብ ጎንደሮች ጊዎርጊስና ብላጂግ ያዋስኑታል፡፡

ንጉስ ፋሲለደስ ለአካባቢዉ የቅማንት ባላባቶች የእርስት መሬታቸዉን ካሳ ከከፈሉ በኃላ አሁን ጎንደር በፊት “ጓኣንደር” ተብሎ በሚጠራዉ ቦታ ላይ የኢትዩጵያ ማዕከላዊ መንግስት መቀመጫ ዋና ከተማ ቤተ-መንግስት ሲቆረቆሩ በወቅቱ ንጉስ ፋሲለደስ በዉጭ ሃገር የኪነ-ህንፃ ጠበብቶች ወይም አርክቴክቶች እየታገዙ በአካባቢዉ የቅማንት ህዝብ ድጋፍና ጥረት ቤተ-መንግስታቸዉን ለማቆም በቅተዋል፡፡ በዚህ ወቅት የቅማንት ህዝብ በጉልበቱና በእዉቀቱ ኖራን ከጭልጋና ከጅብ ዋሻ ጎንደሮች ማርያም አካባቢ፤ ጋባ ከሚባ ቦታ ሲያስመጡ ፤ ደም በቃ የተባለዉ ጠንካራ የእንጨት ዘር ከቅማንቶች ምድር አርማጭሆ ጃኒፈንቀራ ከተባለ ቦታ በማምጣት          ክርስትና የተቀበሉት የቅማንት ልጆች “አምሃራ” ተብለዉ የሚጠሩት የደም በቃ ጣዉላ ይዘዉ እስከ ቤተ-መንግስቱ ተጉዘዉ ሲገቡ፤ የጥንታዊዉን የእነ አብርሃምን ህገ-ልቦና ሃይማኖት ተከታዩች ግን “ግንድ መጣያ” ከሚባል ቦታ ድረስ በማድረስ ወደ አርማጭሆ ይመለሱ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ይህ አርማጭሆ ተብሎ የሚጠራዉ ቦታ የተሰየመዉ በአካባቢዉ ጥንታዊዉ ነዋሪ በቅማንት ህዝብ ነዉ፡፡ ትርጉሙም “ የአንበሳ መኖሪያ ቦታ ወይም ጫካ ማለት ነዉ፡” ምክኒያቱም አካባቢዉ ከፍተኛ የሆነ የዱር እንሰሳት እንደ ዝሆንና አንበሳ በብዛት የነበረበት ቦታ ነዉ፡፡ ይህንን በተመለከተ የስኮቲሺ ተጓዥ ጀምስ ብሩስ Travel to discover the source of the Nile በተሰኘዉ መጽሃፉ ላይ ገልፆታል፡፡ ጀምስ ብሩስ ወ/ሮ አስቴርን አግብቶ በመተማ የንግስት ምንትዋብ ቀረጥ ሰብሳቢ ሆኖ በነበረበት ወቅት ብዙ ጀግና ታመኝ የንግስቷ የቅማንት ወታደሮች እንደነበሩት ጠቅሷል፡፡ ብዙ ጊዜም ጀምስ ብሩስ ቅማንቶችን ከቤተ እስራኤላዊያን ለይቶ አይመለከታቸዉም፡፡ ምክኒያቱም የቅማንቶች ህገ-ልቦና ሃይማኖት በብዙ መልኩ ከቤተ-እስራኤላዊያን የአይሁድ ሃይማኖት ስለሚመሳሰል ጥቁር አይሁዳዊያን እያለ ይጠራቸዉ ነበር፡፡
ንጉስ ፋሲለደስ ቤተ-መንግስቱን ከቆረቆሩ እና የመንግስታቸዉን ስርዓት ሲያዋቅሩ ብዙ ቁልፍ ቦታዎች ለቅማንት ተወላጆች ሰጥተዋል፡፡ ለምሳሌ ቄስ ባጅር የተባሉ ቅማንት አጼ ፋሲልን ጩጌ ማሪያም ላይ አነገሱ በአጼ ፋሲል ዘመነ-መንግስት ጎንደርን ያሽከረክሯት የነበሩ 4 ቅማንት ወንድማማቾች ነበሩ አጼ ፋሲል ለአገዛዝ ያመቸው ዘንድ ጎንደር ክፍለ-ሀገርን ለአራት የቅማንት ጠቅላይ ገዢዎች ከፋፍለው ሰጡዋቸው፡-
1. አዛዥ ቹሳ – አጠቃላይ አርማጭሆን ከከርከር እስከ ሁመራ ድረስ        ያስተዳድሩ ነበር፤
2. አዛዥ ደሩዝ ከጭልጋ እስከ መተማና ቋራ ድረስ ያስተዳድሩ ነበር ከዚያ እያሆ ማሪያም/ጭልጋ/ ተቀበሩ፤
3. አዛዥ ሞላ/ማትቦ/- ከወለቃ ወገራ እስከ ጠገዴ ድረስ ያስተዳድሩ ነበር፤
4. አዛዥ ባህሪን -ከፀዳ-ደንቢያ እስከ ፎገራ ድረስ በማስተዳደር ማክሰኝት ልዩ ቦታው ጭህራ ከሚባል ባህሪ ግንብ ሀውልት አሰርተዋል፡፡
ከጎንደር ስርኦ መንግስት መመስረት በፊት የነበረዉ የሰለሞን ስርኦ መንግስት ነገስታት ወንድ ልጆቻቸዉ እንዳያምጹባቸዉና ጦርነት በቤተሰብ መካከል እንዳይነሳ በመስጋት ነገስታት የሚወልዷቸዉ ወንድ ልጆች ለአቅመ አዳም ከመድረሳቸዉ በፊት ወሎ አምባ ግሸን በተባለ ቦታ በእስራት ያስቀምጧቸዉ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ የነግስታት ቤተሰቦች ወህኒ ቤት በ1530ዎቹ አካባቢ በአህመድ ግራኝ አማካኝነት እንደጠፋና እንደተዘጋ ይታወቃል፡፡ የጎንደር ነገስታት ግን የነገስታት ቤተሰቦች ወይም ለአቅመ አዳም የደረሱ ወንድ ልጆች የሚታሰሩበት ወህኒ ቤት እንዲሆን የመረጡት በቅማንቶች ምድር ጭልጋ “ወህኒ አምባ“ ተብሎ በሚጠራ ቦታ ሲሆን የሚገኘዉምን በሰራባና ነጋዴ ባህር መካከል ግንት ተብሎ በሚጠራዉ ወንዝ ነዉ፡፡
በ1640ዎቹ የኦቶማ ቱርክ ወራሪ ሃገራችን በሱዳን መተማ በኩል ወረራ ባደረገበት ወቅት ጀግናዉ የቅማንት ህዝበ ከንጉስ ፋሲለደስ ጋር በመሆን ሃገር ወዳድነቱን አስመስክሯል ፤ታላቅ ጀብዱንም አሳይቷል፡፡ በወቅቱ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀዉ የቱርክ ሰራዊት በመጀመሪያዉ ቀን የንጉስ ፋሰሊደስን ጦር በተወሰነ መልኩ አሸንፊ እና በጦርነቱም ንጉስ ፋሲለደስን ማርኮ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ያለ መሪ ተብታትኖ ሊቀር የነበረዉን የፋሲለደስ ጦርና  የሃገራችንን ዳር ደንበር እንዳይደፈር በመከላከል ትልቅ ሚና የተጫወቱት  የንጉስ ፋሲለደስ የመተማና አካባቢዉ አስተዳዳሪነ መሪ የነበሩት ቅማንቱ ራስ ድሩዝ ነበሩ፡፡ እንደሚታወቀዉ ንጉሱ ከጠንካራዉ ፈረሳቸዉ ዞብል ጋር ነበር የተማረኩት ፤ነገር ግን ቱርኮች ዞብልን በተደጋጋሚ ለመጋለብ ሞክረዉ ከኮረቻ ወደ ምድር እያወረደ እየፈረጣቸዉ ስለነበር ንጉሱን ከታሰሩበት ጠርተዉ ጋልበዉ እንዲያሳዪቸዉ ሲጠየቁ ንጉስ ፋሲለደስ አጋጣሚዉን በመጠቀም ታመኙን ዞብል ፈረሳቸዉን ሽምጥ በመጋለብ  ወደ ወገን ራስ ድሩዝ  ጦር ተቀላቀሉ፡፡ በሰራዊቱም ዉስጥ ትልቅ የሞራል መነቃቃት ፈጠረ፡፡ የንጉሱ  ጦር በማግስቱ በራስ ድሩዝ  እየተመራ ወራሪዉን ቱርክ ድል በመንሳት የሃገሩን ዳር ደንበር አስጠብቋል፡፡
ታላቁ ንጉስ እያሱ አዲያም ሰገድ ከሞቱ በኃላ ከ1704 እስከ 1721 ድረስ በነበረዉ በጎንደር ስርኦ-መንግስት በነገስታት መካከል በነበረዉ አለመግባባት እና የስልጣን ሽኩቻ ወቅት የቅማንት ህዝብ ለስርኦ-መንግስቱ ሰላምና መረጋገት ትልቅ ሚና ነበረዉ፡፡ በተለይም በወቅቱ ከወሎ የጁ ኦሮሞ እና የትግራይ ባላባቶች የጎንደር ስርኦ-መንግስት እንዲፈርስ የተለያየ ጥረት ሲያደርጉ ጀግናዉና ሃገር ወዳዱ የቅማንት ህዝብ ስርኦ-መንግሰቱን ከመፈራረስ ታደጓል፡፡ በንግስት ትዋበት ቋረኛዋ ዘመንም የቅማንት ህዝብ ቀጥተኛ ፖለቲካዊ ተፅዕኖና ተሳትፎ ነበረዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ ንግስቷ በቋራ የቅማንትና የቤተ-እስራኤል ተወላጅ ስለነበሩ፤የቋራ ቅማንት ቋረኛ የተበላዉ የቅማንትኛና የአገዉኛ ቋንቋ በጎንደር ቤተ -መንግስት (በቁስቋም ቤተ-መንግስት) ዉስጥ ይናገሩ ነበር፡፡ በነገራችን ላይ ቋራ ማለት በቅማንትኛም ይሁን በአገዉኛ “ፀሐይ” ማለት ነዉ፡፡ አሁንም ድረስ ይህንን ቋረኛ የተባለዉ የቅማንትኛና የአገዉኛ ቋንቋ በእስራኤል አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይነገራል፡፡
ከ1769-1855 ዓ.ም ድረስ የጎንደር ስርኦ-መንግስት ሲዳከምና ሲፈራርስ ሃገር ወዳዱ የቅማንት ህዝብ በጎጥና በብሄርተኝነት ስሜት ሳይዘፈቅ ከማንኛዉም ዘመነ መሳፍንት ባለባቶች ጋር ሳይወግን የሃገር አንድነት ስሜቱን በዉስጡ ይዞ ጠብቋል፡፡                           ለዚህም ማሳያ በዚህ የዘመነ መሳፍነት ዘመን ወቅት የስሜን ህዝብ ከራስ ዉቤ ጋር፤ የደብረ ታቦርና ጋይንት ህዝብ ከእነ ራስ አሊ ዘሮች ጋር በመሆን ለ80 ዓመት በላይ ፤የጎጃም ህዝብ ከራስ ጎሹ ጋር በመሆን ወግኖ በጎጠኝነት ስሜት አካባቢዉን እና ቀየዉን መስሎና ሆኖ ሲኖር ኑሯል፡ ነገር ግን ጀግናዉ ሃገር ወዳዱ የቅማንት ህዝብ ግን ከዚህ አይነት ጠበብነት ራሱን አርቆ በመጨረሻም ጀግናዉን ደጃዝማች ካሳ ኃይሉን መርጦ ለሃገር አንድነት ዉህደት ሲቆም በታሪክ ታይቷል፡፡
በዚህ ዘመነ መሳፍንት ዘመን የቅማንት ህዝብ የዘመኑን ጎጠኝነት ሳይቀበል፤በዘር ሳያምን ፤በአንድ ኢትዩጵያዊነት አምኖ ከማንም የዘመኑ ባለባቶች እና መሳፍንቶች ጋር ሳይወግን ሃገር ወዳድነቱን አስመስክሯል፡፡ በዚህ ዘመንም በተለይም የየጁ ስርኦ መንግስት መቀመጫዉን በደብረታቦር አድርጎ በነበረበት ወቅት በቅማንት ምድር (በአሁኑ አብዛኛዉ ምዕራብ ጎንደር) ላይ በቀጥታ አንድም ጊዜ ሳያስተዳድር ፤በአግባቡ ግብር ሳይሰበስብ ነዉ መንግስቱ የወደቁዉ፡፡ እንዲያዉም አብዛኛዉን ጊዜ ይህ ቦታ የሽፍታና የወንበዴ መሰባሰቢያ ስለነበር ለየየጁ ስርኦ መንግስት ፤ ለስሜን ባለባቶች የራስ ምታት የነበረ በኃላም ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ የመሰለ ጀግና ሃገር ወዳድ ፀረ- ክፍፍልንና ጎጠኝነትን የተቃወመ ኃይል ያወጣ ቦታ ሁኗል፡፡
በዘመነ መሳፍንት ወቅት (ከ1769-1855) ሃገራችን በዘር ፤በጎጥ በተከፋፈለች ወቅት የቅማንት ህዝብ ከማንም በላይ ከደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ጋር በመሆን ሃገራችን አንድነት ዳግም እንዲመለስ ብሄራዊ ጀግንነት ፈጽሟል፡፡ በተለይም ከአባ ታጠቅ ካሳ ጋር በመሆን ከሽፍትነት ጀምሮ እስከ ማዕከላዊ መንግስት እስከ መሰረቱበት ሰዓት ሚናቸዉ ከፍተኛ ነበር፡፡ ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በወ/ሮ መነንና ልጃቸዉ በታላቁ ራስ ዓሊ ላይ ሲያምጹና ሲሸፍቱ ብዙ ሽህ የቅማንት ልጆች ይዘዉ በቅማንት ልጆች በእነ ደጃዝማች አይክል ኮልባ ፤ባላምባራስ ገልሞ ፤ ራስ ቢትወደድ ዋሴ ተመርጠዉ ….“ምንም እንኳን አንት ገና ወጣት የ25 ዓመት ልጅ ብትሆንም ወኔህና ጀግንነትህ ፤የሃገር አንድነት ፍቅርህ ልዩ ስለሆነ ምራን ” ብለዉ የተከተሏዉ፡፡ ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ለመጀመሪያ ጊዜ የሸፈቱት ከጎንደር ቋራ ሳይሆን ወደ ጭልጋ ብዙ ጭፍራዎችን አስከትለዉ ነበር፡፡ በጭልጋ የቅማንት ባላባቶች ተቀብለዉ በሚስጠራዊ ዋሻ ወይም ምሽጋቸዉን ቤዛሆ ተብሎ በሚጠራ ቁልፍ እስትራቴጃዊ ወታደራዊ ጥቅም የነበረዉ ከአይከል ከተማ ከ5 ኪሎሜትር ርቀት በሚገኝ ለቆላዉና ለደጋዉ ወደ ዳዛ፤ጫቆና አዳኝ ሃገር ለመዉረድ በሚያስችል ቦታአስቀምጠዋቸዋል።
ከዚህም በኃላ ከቤዛሆ ምሽጋቸዉ ወጥተዉ ብዙ የቅማንት ጎበዝ አስከትለዉ ቁልፍ ወታደራዊ ጥቅም ወዳለዉ የጀግኖቹ የማር ቤቴ ቅማንቶች ቦታ ዳዛና ጫቆ ያመሩት፡፡ በዚህ ወቅት ባለቤታቸዉ ተዋበች አሊ አብራ ተጉዛለች፡፡ ከዚህ ላይ አንድ ነገር ላስታዉሳችሁ ወደድኩ እሱም ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ እተጌ ትዋበች አሊን ከማግባታቸዉ በፊት ገና 18 ዓመት እድሜያቸዉ ክልል በአካባቢዉ ወግ ባህል መሠረት የጭልጋዉን ወህኒ አምባ ባለባት ታዋቂ ሽፍታ ቅማንት አቶ እንግዳወርቅ ሴት ልጅ ወ/ሮ ገሰሱን አግብተዉ ሁለት ልጆች መሸሻና አልጣሽ የሚባሉ ወልደዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ አለቃ ዘነበ የፃፉትን ማንበብ ትልቅ እዉቀት ይሰጣል፡፡
ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ በዚህ የጫቆ ሽፍትና ዘመናቸዉ ሰዓት ከሲራራ ነጋዴዎች ብዙ ንብረት እየቀሙ ለድሃ ገበሬዎች ያከፋፍሉ ነበር፡፡ በተለይም የወ/ሮ መነንና ባለቤታቸዉ አጼ ዩሃንስ ሶስተኛ እንዲሁም የልጃቸዉ የታላቁ ራስ ዓሊ ግብርና ቀረጥ ሰብሳቢዎችን ገንዘብና ንብረት በመቀማት ለድሆች ይሰጡ ነበር፡፡ ይህ ድርጊት እቴጌ መነንን ከሽፍትነቱ በላይ በጣም አስቆጣ፡፡ እቴጌዋም በጎንደር ከተማ ዙሪያ ያሉ ቅማንቶች ላይ በተደጋጋሚ ግብር ጣሉ፡፡ በመጨረሻም እቴጌ መነን ከቤተሰቦቻቸዉና ከጦር መሪዎቻችዉ ጋር መክረዉ ከደብረታቦርና ከጋይንት ከታላቁ ራስ ዓሊ ጦር ተወጣጥቶ በጦር መሪዉ በደጃዝማች ወንድይራድ አማካኝነት ወደ ጫቆ ጦር አዘመቱ፡፡ በዚህም ሰዓት ደጃዝማች ወንድይራድ ከእቴጌ መነን ፊት በጎንደር ቤተ-መንግስት በር ላይ ፎክሮ ይህንን ..“ቆለኛ የፍየል እረኛ…… የኮሶ ሸምጣጭ ልጅ ማርኬ የፍጥኝ አስሬ ከፊትዎ አቀርባለሁ .. በማለት ዝቶ ዘመተ.. ”
የደጃዝማች ወንድይራድ ሰራዊት በጀግናዉ የማር ቤቴ ቅማንት ጫቆ ላይ ድባቅ ተመትቶ ወንድይራድም ተማረከ፡፡ ደጃዝማች ካሳም እናቴ ከገቢያ ሳይሸጥላት የተረፈ ኮሶ ስላለ ለአንተ የሚሆን ምግብ ስለሌለን ኮሶዉን ፈጭተህ ዉሰድ ብለዉ ኮሶ አስደቁሰዉ እያስበጠበጡት፡፡ የሚከተለዉን ግጥም ገጠሙለት፤-
የእንቆቆ ልጅ እንቆቆ የኮሶ ልጅ ኮሶ
በሽታዉ ያሽራል እንኳንስ ተቀምሶ፡፡
ኮሶ ሻጭ ናት ብሎ ማነዉ የነገረህ?
በል እንካ ቅመሰዉ አይጎፍንን አይክፋህ፡፡
የጀግናዉን እናት የኔን የመይሳዉ
ኮሶ ሽያጭ ናት ብሎ የነገረህ ማነዉ?
ይልቁንስ ይህዉልህ በል እንካ ተጋተዉ፡፡
እያሉ አባ ታጠቅ ሲያስጠቱት የጫቆ ቅማንት ይህንን አይቶ በመሳቅ በማፊዝ እንዲህ ብሎ ለደጃዝማች ወንድይራድ ገጠመለት፡፡
እንቆቆና ኮሶ ሲጠጣ ለዉሶ
አየነዉ ወንድይራድ ሲፈጭ ተጎንብሶ፡፡
ወዳጀ ወንድይራድ ምነዉ የማይኮራ
ነዉር አይደለም ወይ መግባት በሴት ስራ፡፡
ወዳጀ ወንድይራድ የሚመክረዉ ጠፍቶ
ሲፈጭ አደረ አሉ በሴት ስራ ገብቶ፡፡
ከዚያም ደጃዝማች ወንድይራድ የጠጣዉ ኮሶ ከልክ በላይ ሁኖ ሌሊቱን ገድሎት አደረ፡፡ ከዚህ በኃላ እንቆቆዉ ቅማንት የሚለዉ ቅጽል ስም በአብዛኛዉ ለቅማንት ህዝብ የተሰጠዉ ከዚህ ታሪካዊ ድል በኃላ ነበር፡፡ በዚህም ድል የወ/ሮ መነንና ባለቤታቸዉ አጼ ዩሃንስ ሶስተኛ እንዲሁም የልጃቸዉ የታላቁ ራስ ዓሊ ክፉኛ ተደናገጡ፡፡ የዚህን አስደናቂ ታሪክ በተጨማሪ ከጳዉሎስ ኞኞ አጼ ቴዎድሮስ የሚለዉ ታሪካዊ መፅሃፍ እና ግርማ ያሬድ የፃፈዉን የጎንደር ታሪክ ዉስጥ ያገኙታል፡፡
ከዚህ የጫቆ የሽፍትና የ5ዓመት ጊዜያቸዉ በኃላ ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ ሁላችንም ወደምናዉቀዉ ወደ ቋራ ከታመኝ የቅማንት ልጆች ከጦር መሪያቸዉ ከባላምባራስ ገልሞ ጋር ሁነዉ ያመሩት፡፡ በዚህ ወቅት ግን ባለቤታቸዉን ወ/ሮ ተዋበችን ይዘዉ መንቀሳቀሱ ስለማያመች ከዘመዳቸዉ ደጃዝማች አይከል ኮልባ መቀነት በሚባል ቦታ በዋሻ ዉስጥ ለ8 ዓመት ያላነሰ አጼ ቴዎድሮስ በደረስጌ ማርያም ንጉሰ ነገስት ሆነዉ እስከሚነግሱ ድረስ ተደብቃ እንድትቀመጥ አደረጉ፡፡ የዚህን ድንቅ ታሪክ በተመለከተ ከጳዉሎስ ኞኞ አጼ ቴዎድሮስ መፃህፍ ዉስጥ  በሚያምር የታሪክ አደራደር ያገኙታል፡፡
የቅማንቱ የባላባት ልጅ ባላምባራስ ገልሞ ደጃዝማች ካሳ ኃይሉን ከመምረጥ ጀምሮ በተለያዩ ቦታዎች የማይነጣጠሉ ፤የሚከባበሩ፤ እንደ ወንድም የሚዋደዱ ፤የሚተማመኑ ነበሩ፡፡ ባላምባራስ ገልሞ ከካሳ ጋር በመሆን እስከ መጨረሻዉ ንግሳቸዉ ድረስ በተለያዩ ቦታዎች የተዋጉ ያዋጉ ጀግና ቆራጥ መሪ ሲሆኑ ለደጃዝማች ካሳ ኃይሉ በሽፍትና ዘመናቸዉ ቁልፍ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡ ደጃዝማች ካሳ ኃይሉ በተደጋጋሚ ለወታደሮቻቸዉ “እኔ ብሞት ሊተካይ የሚገባዉ ገልሞ ነዉ እያሉ ሁሉ ይናገሩ ነበር፡፡” የባላምባራስ ገልሞ ጅግንነት የተመሰከረበት ሱዳን ዉስጥ ደባርቄ ከተባለ ቦታ የቱርክ ሰራዊትን ለማጥቃት በተደረገዉ፤ ራስ ዓሊን በአይሻል በአሸነፉበት ቦታ እና የጎጃሙን ንጉስ ደጃዝማች ጎሹን ለመዉጋት ጉራአምባ በተባለዉ ቦታ ሲሆን በተለይ በጉራአምባ የአባ ታጠቅ ካሳን ጦር የመራዉ ባለምባራስ ገልሞ ነበር ታዲያ በዚህ ጦርነት የጎጃም ጦር ብዛት ስለነበረዉ ገልሞ ክፉኛ ቆሰለ፤ አቆሳሰሉም ከጠላት የተወረወረ ጦር ከቀኝ ጉንጫቸዉ በስቶ በግራ ጉንጫቸዉ ወጥቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ጀግናዉ ቆራጡ ባላምባራስ ገልሞ ደሙን በአፉ እያዘራ ጦርነቱን ቀጠለ ፤ ከዚያም በእርቀት ጦርነቱን ሲመለከት የነበረዉ የካሳ ጦር የገልሞ ጦር በቁጥር እንደተበለጠ ሲያዉቁ ኃይሉን አጠናክሮ እየፎከር በመግባት ደጀዝማች ጎሹን መትተዉ ጣሉት፤ በዚህ ሰዓት የጎጃም ጦር ተፈታ፡፡ ከጦርነቱ በኃላ ለካሳ የገልሞ ለጊዜዉ መሰወር  አስጨንቆት ነበር ፤ የተወሰኑ ወረኞችም ገልሞ ሸሽቷል እያሉ አስወሩ አዝማሪም በግጥም ከአባ ታጠቅ ፊት እንዲህ ገጠመች፡፡
አይሸሽም ያልከዉ ገልሞ እንኳን ሸሸ
የደንቢያን ግራር እያበላሸ፡፡
በኃላም ገልሞ በጣም ተዳክሞና ብዙ ደም ፈሶት ጦሩን በጥርሱ እንደነከሰ ወደ አባ ታጠቅ መጥቶ ተገናኙ፡፡ ደጃዝማች ካሳ ራሱ በእጁ ከገልሞ ጉንጭ ጦሩን ነቅሎ አወጣለት፡፡ ከዚያም ወደ አዝማሪዋ አባ ታጠቅ ዘወር ብሎ እንዲህ አለ፡-
አብለሻል እንጅ እዉነቱን አላልሽም
በዙበት እንጅ ገልሞስ አይሸሽም፡፡
የዚህ አስገራሚ ሙሉ ታሪክ ገድል ከጳዉሎስ ኞኞ አጼ ቴዎድሮስ ያገኙታል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ ከነገሱ በኃላ ባላምባራስ ገልሞ የንጉሱ ምስለኔ በመሆን ከቋራ እስከ አርማጭሆ ያለዉን ሃገር ( ጭልጋን፤ ደንቢያን፤ መተማን፤ አለፋ ጣቁሳን) አስተዳደሩ፡፡ ስለዚህ ታሪክ አለቃ ዘነበ ጽፈዋል፡፡
በንጉስ ቴዎድሮስ አስተዳዳር ዘመን ከ1855-1868 ዓ.ም ድረስ በተለያዩ ቁልፍ ቦታዎች ዉስጥ ለሃገር አንድነት፤ እድገት፤ ብልፅግና ዘር ጎጠኝነት ሳያጠቃቸዉ የሚሰሩ የነበሩ ብዙ ሽህ የቅማንት ልጆች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ በአጼ ቴዎድሮስ መንግስት ደስተኛ ያለሆኑ ባላባቶች ቀሳዉስት ብዙ ነበሩ፡፡ በዚህም ምክኒያት አጼ ቴዎድሮስ ለመግደል ፤የመንግስታቸዉን ስርዓት ለመጣል የሚያሴሩ ብዙ ባለባቶች መኳንቶች ስለነበሩ ተይዘዉ በመቅደላ ይታሰሩ ነበር፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ምክኒያቶች ወደ ሃገራችን ገብተዉ ቃላቸዉን ለንጉሱ ያፈረሱ አዉሮፓ ሃገራት ዜጎች  ወይም መልዕክተኞች ተይዘዉ በሚታሰሩት የመቅደላ እስር ቤት ዋና የእስር ቤቱ የበላይ ኃላፊ የነበሩት ታማኙ ወገናቸዉ ቅማንቱ ራስ ቢትወደድ ዋሴ የደጃዝማች ቢተዋ ወላጅ አባት ፤ የቀኝ አዝማች ተሰማ አስረሳ አጎት ናቸዉ፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ይህንን ያደረጉበት ምክኒያት ከዚህ በፊት የተለያዩ ጠላቶቻቸዉ ተይዘዉ ሲታሰሩ እርሳቸዉ በዘመቻ ምክኒያት ከቦታ ቦታ ወሎ ሸዋ ሲዘዋወሩ ባልታወቀ ምክኒያት እነዚህን ጠላቶቻቸዉን ያስመልጧቸዉ ነበር ፡፡ በኃላ ደጃዝማች ዋሴን ዋና ሹም አድርገዉ ከሾሙ በኃላ ግን ምንም አይነት እስረኛ ሳያመልጥ ቀርቷል፡፡ ስለ ታመኝነታቸዉና ቅንነታቸዉ የአዉሮፓ እስረኞች ሁሉ የመሰከሩላቸዉ እንደሆነ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ አጼ ቴዎድሮስና የኢትዩጵያ አንድነት በሚለዉ መጽሃፋቸዉ “….ራስ ቢትወደድ ዋሴ የቅማንት የጭልጋ ባላባት ሙስና የማይወዱ … የንጉሱ እዉነተኛ ባለሟል… እጃቸዉን እጥፍ ዘርጋ በማድረግ ንግግር የሚችሉ ” ብለዉ መስከረዉላቸዋል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ በዘመናቸዉ ከነበረዉ አስፈና ኃያሉ 100,000 ጦራቸዉ ዉስጥ በመጨረሻ በመንግስታቸዉ መዉደቂያ ሰዓት 10,000 ብቻ ጦር ነበራቸዉ፡፡ ከዚህም ዉስጥ አብዛኛዉ ቅማንቶች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡ መቅደላ በእንግሊዝ ጦር ጥቃት በደረሰበት ሰዓት ብዙ ወታደሮቻቸዉ በተለይም የወሎ ሰቆጣ ደብረታቦርና ጋይንት  አካባቢ ሰዎች ከዷቸዉ ፡፡ በኃላ ዙሩዉ ከጦርነቱ የተረፈዉ የንጉሱን ጦር ቅማንቶችን ጨምሮ ወደ ጎንደር ሲመለሱ እናተ ናችሁ በፊት ከዚያ እብድ ንጉስ ጋር ሁናችሁ የወጋችሁን ፤ቤታችንና ንብረታችን ያቃጠላችሁብን በማለት ተበቀሏቸዉ፤ ብዙዎችንም ገደሏቸዉ፡፡ በተለይ እንደ ሪቻርድ ፓንክረስት The Abyssinian Campaign , Ethiopian observer ገለፃ  “.. አጼ  ቴዎድሮስ ብዙ ሽህ ወታደሮቻቸዉ ሲከዷቸዉ እስከ መጨረሻዉ ድረስ በታማኝነት ከሞቱም በኃላ ይዋጉ የነበሩት የቅማንት ጭፍራ ወታደሮች ናቸዉ ሲሉ ይገልፃሉ፡፡”
ምንጭ፡ 
ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ ,የኢትዩጵያ ታሪክ ከአጼ ልብነ ድንግል እስከ አጼ ቴዎድሮስ
ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ, አጼ ቴዎድሮስና የኢትዩጵያ አንድነት
አለቃ ዘነበ ,የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ
ፕሮፊሰር ሲ ጋመስ , የቅማንት ህዝብ ታሪክ
James Quirin , The Kemant peasant class
የትይንተ ጎንደር መፅሄት
ነጋ ጌጤ ,የቅማንት ህዝብ አጭር ታሪክ
ገሪማ ታፈር , አባ ታጠቅ ካሳ የቋራዉ አንበሳ
አለቃ ወልደ ማርያም, የአጼ ቴዎድሮስ ታሪክ
ያሬድ ግርማ , የጎንደር ታሪክ
ግራሃም ሃንኮክ ,The sign and the seal
ጀምስ ብሩስ ,Travel to discover the source of the Nile
ሪቻርድ ፓንክረስት ,The Abyssinian Campaign , Ethiopian observer
ፕሮፊሰር ሰለሞን አዲስ  ,የጎንደር ታሪክ ከጣሊያን ወረራ በኃላ አ.አ.ዩ የማስተርስ ጥናታዊ ፅሁፍ
በሚቀጥለዉ ፅሁፊ “የቅማንት የደንበር ጀግኖች እና የማህዲስት ወረራ ከ1870-1888ዓ.ም ” በሚል እርዕስ እመለሳለሁ፡፡
ባላምባራስ ነጋሽ ከመተማ

Leave a Reply